አዲስ አመትን ሳስብ መቼም የማይረሳኝ ነገር አዲስ ልብስ እና ጫማ ተገዝቶልን እኔና ወንድሞቼ መስከረም 1 አልነጋ ብሎን በዋዜማው አዲስ የተገዛልንን ጫማና ልብሳችንን ለብሰን አልጋችን ላይ እንተኛ ነበር፡፡ እንዲሁም አዲሱን አመት ስናስብ ከሁላችንም አይምሮ የማይጠፋው ነገር የሴት ልጆች የአበባ አየሽ ወይ ዘፈንና መዝሙር ነው፡፡  ሁላችንም እንደምናውቀው ኢትዮጵያ የብዙ ብሄር ብሄረሰብ እናት እንደመሆኗ ሁሉም ብሄርና አካባቢ የራሱ የሆነ አዛሄምና ጭፈራ አለው፡፡እኔም ለዛሬው እኔ ያለፍኩበትን የአበባ አየሽ ወይን

ትውስታ ላወጋችሁ ወደድኩ…. ገና የክረምቱ መባቻ ሲደርስ ሁሉም በየ ፊናው ዝግጅቱን ይጀምራል፡፡ የተለያዩ ሴት ልጃ ገረዶችና ህጻናት የአበባ አየሽ ወይ ዘፈንና መዝሙር ልምምዳቸውን ይጀምራሉ፡፡ ያው ዘፈንና መዝሙር የምላችሁ 2 አይነት አዛዜም ስላለው ነው መንፈሳዊና አለማዊው ማለቴ ነው፡፡ አንዳንዶች አበባ አየሽ ወይን በአለማዊው መንገድ ወይንም በዘፈን እንዲህ በማለት ያዜሙታል …….                      

                                      አበባ አየሽ ወይ   ለምለም

                                      ባለንጀሮቼ         ለምለም

                                      ግቡ በተራ         ለምለም

                                      እንጨት ሰብሬ    ለምለም

                                      ቤት እስክሰራ      ለምለም

                                      እንኳን ቤትና      ለምለም

                                      የለኝም አጥር      ለምለም  

                                      እደጅ አድራለሁ   ለምለም

                                      ኮከብ ስቆጥር      ለምለም

                                      ኮከብ ቆጥሬ       ለምለም

                                      ስገባ ቤቴ          ለምለም

                                     ትቆጣገኛለች       ለምለም

                                     የእንጀራ እናቴ     ለምለም

         አደይ የብር ሙዳይ ኮለል በይ ሽት አበባ ሽት አበባዬ……. አዬ ሽት ሽት አበባ ስትለኝ ከርማ…... አዬ ሽት አበባዬ

       ከብረው ይቆዩ ከብረው በ አመት ወንድ ልጅ ወልደው ከብረው ይቆዩ ከብረው!!! እያሉ እየተቀባበሉ ሲያዜሙት………

                         የቤተክርስትያን መዘምራኑ ደግሞ………

  እሰይ ደስ ደስ ይበለን…… ደስ ደስ ይበለን አዲሱ አመት መጣልን ደስ ደስ ይበለን

  ደስ ብሎን መጣን ደሰ ብሎን ጌቶች አሉ ብለን………………

                                   እንቆቅልሹን        ንግስት

                                   ልትፈትል ሄዳ      ንግስት

                                   ንግስተ አዜብ       ንግስት

                                   እናት ማክዳ         ንግስት

                                   በልቧ ያለውን       ንግስት

                                   አጫወተችው        ንግስት

                                   አስቀምጣ አበባ      ንግስት

                                   እያሳየችው           ንግስት

ንግስት ሆይ ለጥያቄሽ ጥበብ አለሽ…………ኢትዮጵያ በታሪክሽም ጥንታዊት ነሽ………. እያሉ መንፈሳዊ በሆነ አለባበስና አዘማመር ይዘምራሉ፡፡ መንፈሳዊውን ነገር ያነሳሁላችሁ እኔም ከልጅነቴ ጀምሮ በዚሁ በመንፈሳዊው የአበባ አየሽ ወይ መዝሙር ስላደኩና ስለዞርኩ ነው ፡፡ አቤት ግን ልጅነት እንዴት ደስ ይላል!!!! የሚገርማችሁ ሁል ጊዜ አበባ አየሽ ወይን ለመዘመር ስናስብ ገንዘብ ሰብሳቢ ተደርጌ የምመረጠው እኔ ነበርኩ ነጭ የሀበሻ ቀሚሴን ለብሼ ጸጉሬን ሹሩባ ተሰርቼ ነጯን ጫማዬን አድርጌ መሶበ ወርቅ ወይም ገንዘብ መሰብሰብያዬን መሶብ እይዝና ከ ጠዋቱ 12፡00 ጀምረን ቤታችን የምንገባው ማታ 3፡00 ነበር፡፡ ገንዘቡን ደግሞ ሰብስበን እንደ ሌሎቹ ለራሳችን መከፋፈል ሳይሆን ለቤተክርስትያን ነበር የምንሰጠው  በቃ ምን ልበላችሁ  የእንቁጣጣሽ በዐል ሲመጣ በየ ሰው ቤቱ እየዞርን ሰው ሁሉ ከ ሳንቲም ጀምሮ እስከ 300 ብር፣ዳቦ፣ቆሎ፣ምግብና መጠጥ በቻለው አቅሙ ያደርጋል፡፡ሁሌም የልጅነቴን የአበባ አየሽ ወይ ዙረት መቼም አረሳውም፡፡ ደግሞ ድካሙስ ብትሉ በንጋታው እኮ ለመነሳት በጣም ነበር የሚከብደን…. ያው እንደ በፊቱ አይደለም እንጂ አሁንም ልጆች የሀበሻ የባህል ልብሳቸውን ለብሰው አበባ አየሽ ወይ እያሉ ሲዞሩ ትንንሽ ወንድ ልጆች ደግሞ የሚያማምሩ አበባ ስለው ሲያዞሩ…. የሀገራችን ሜዳው ሸንተረሩ አረንጓዴ ሆኖ በዚህ አረንጓዴአማ ገጽታ ላይ በአደይ አበባ አሸብርቆ ሲታይ አቤት……. ኢትዮጵያ ሀገሬ እንዴት ውብ እንደሆነች!!!!! በሌላው በኩል ደግሞ አዲሱ አመት ሲመጣ ያለው የገበያው ትርምስ የማይረሳው ነገር በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በዐልን ከቤተሰባቸው ጋር ለማሳለፍ ወደ ሀገራቸው ሲገቡ ያለው የኤርፖርት ግርግርና መጨናነቅ…. በየ መናኸርያው ያለው የሰው ሰልፍና በዐልን አስታኮ የእያንዳንዱ ነገር የዋጋ ጭማሪ በጣም ያስገርማል!!!…. የ እናቶቻችንና የሴት እህቶቻችን እያንዳንዱን የቤት እህል ከማዘጋጀት ጀምሮ ያለው ድካም፣ የቤት ፅዳት ፣እና ዕቃ መግዛት ያው ታውቃላችሁ አይደል? አዲስ አመት ሲመጣ ቤታችንን ለየት ማድረግና አዲስ ነገር መፍጠር እንወዳለን ውይይ ያለው ልፋትና ድካም!!!! በቃ የቱን ዘርዝሬ የቱን ልተውላችሁ የአዲስ አመት ተውስታዬ ብዙ ነው……ያው ሌላ ጊዜ በሌላ ትውስታ እስከምንገናኝ በመጨረሻም እንደው ምክር ቢጤ ልለግሳቸሁና ላብቃ ሁሌም በዐል ሲመጣ አንዳንዶች በመጠጥ ስካርና አላስፈለጊ በሆነ መንገድ በዐሉን ሲያሳልፉ ይስተዋላል… ያ ከሚሆን ግን በአግባቡና ስረዐት ባለው መልኩ ቢሆንና የተቸገሩትን እንዲሁም የሚረዳቸው አጥተው  በየ ቦታው ያሉትን እያሰብንና እየረዳን በዐሉን ብናሳልፍ መልካም ይመስለኛል፡፡ በተረፈ ግን መልካም በዐል እንዲሆንላችሁ ምኞቴ ነወ፡፡                 

                                                 ሰላም!!!